እኛ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች የመንፈሳዊት አውድ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች በአብ ስም አምነን አብን ወላዲ ብለን በወልድ ስም አምነን ወልድን ተወላዲ ብለን በመንፈስ ቅዱስ ስም አምነን መንፈስ ቅዱስን ሰራፂ ብለን ምንም ለአጠይቆ አካላት ሦስት ብንል በባህሪይ@ በህልውና@ በፈቃድ@ በመለኮት@ በእግዚአብሔርነት አንድ አምላክ ብለን አምነን በአንድነት በፍቅር እና በስምምነት እንኖር እንደነበር ትናንት አንድ ሆነን ያነፅናቸው እኒህ ግሩማን ህንፃ አብያተ ክርስቲያናት@ አያሌ ቅዱሳት መፃህፍት@ በክብር ተቀብለን በፍቅር አስተናግደን ሸኝተናቸው የነበሩ እነዚያ የቅዱስ ገብርኤል እንግዶች በአንድ ወቅት አንድ እንደነበርን ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡
ነገር ግን ዛሬ ታሪክ በመጥፎ ተለውጧል፡፡ የመልካም ምግባር እና የትህትና ጠላት የትእቢት እና የሐሰት አባት ጠላት ዲያብሎስ ጥንት በሥጋ ከይሲ ተሰውሮ ገነት በመግባት አዳም አባታችንን እንዳሳተው ሁሉ ዛሬም ገንዘብን በሚያመልኩና በፈቃደ አምላክ ሳይሆን በፈቃደ ሥጋ በሚመሩ በአንዳንድ አገልጋዮች ልቦና ተሰውሮ ወደ ምእመናን ዘልቆ በመግባት ሰፊ ልዪነትን ፈጥሯል፡፡ እነዚህ አገላጋዮች ሃይማኖትን በመበረዝ ኦርቶዶክሳዊውን አስተምሮና ስርዓተ ቤተ ክርስቲንን በድፍረት በማፋለስ አንድ የነበረና የአንድ ከተማ ነዋሪ ህዝብን የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ልጆችን አንድነት ወደ ሁለትነት መዋደድን ወደ መጠላላት መደጋገፉን ወደ መጠላለፍ እንዲያመራ አድርገዋል በዚህም ታሪክ ይቅር የማይለው ታላቅ በደል በህዝብ እና በቤተ ክርስቲያን ላይ ፈፅመዋል፡፡ ዛሬም እየፈፀሙ ነው ፡፡
ይህ ታሪክ ለኛ ለኢትዮጵያውያን በተለይም ኦርቶዶክሳዊ ለሆንን ለኛ ለሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች አንገት የሚያስደፋ ጉዳይ ነው የተወደዳችሁ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ይህ የጥላቻና የመለያየት ታሪክ ተለውጦ ቀድሞ የነበረው ፍቅርና አንድነት ይመለስ ዘንድ እንዲሁም አፅራረ ቤተ ክርስቲያን እጃቸውን ከቤተ ክርስቲያን ላይ ያነሱ ዘንድ ሁላችሁም ለፀሎት እና በፀሎት ተነሱ፡፡ ‹‹ ማንም ሳይጠራጠር በእምነት ይለምን›› እንዳለ ያዕ 1-6
የተወደዳችሁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ 16-13
‹‹ ንቁ በሃይማኖት ቁሙ ብሏልና ሁላችሁም›› ትክክለኛውን እውነት በመረዳት ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነትና ለኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖታችን ክብር እያደረግን ላለነው መንፈሳዊ ትግል ከጎናችን እንድትሰለፉ እያሳሰብን ከዚህ በመቀጠል ስለአላማችን እና አቋማችን በጥቂቱ ለመግለጥ እንሞክራለን፡፡
አንደኛ
እኛ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወይም በትግል አጀንዳችን ውስጥ የግለሰብ ደጋፊም ሆነ ተቀዋሚ አይደለንም በፍፁም ግለሰብ አጀንዳችን አይደለም; ፖለቲካም አጀንዳችን አይደለም፡፡ ነገር ግን በግልም ይሁን በቡድን በማንም ይሁን በማን በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈፀምን ማንኛውንም አይነት መተላለፍ (ወንጀል) ቅ/ጳውሎስ በ2ኛቆሮ 4÷16-18 ‹‹ ስለዚህ አንታክትም ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን እለት እለት ይታደሳል ›› እንዳለ እኛ ግፍአ ሰማእታትን ሞተ ወልደ አግዚአብሔርን እያሰብን ሳንታክት ሰማያዊውን ዋጋ ተስፋ በማድረገግ የመጣውን መከራ በሙሉ በፀጋ በመቀበል ወንጀልን እና ወንጀለኛን እንቃወማለን፡፡
ሁለተኛ
አባቶቻችን ጌታ በዮርዳኖስ ከተጠመቀባቸው በርካታ ምክንያቶች መካከል አንዱን እንዲህ ብለው ተርጉመው አስተምረውናል ዮርዳኖስ ከላይ ነቁ አንድ ነው ዝቅ ብሎ በደሴት ይከፈላል ከታች በወደብ ይገናኛል፡፡ ዮርዳኖስ ከላይ ነቁ አንድ እንደሆነ የሰው ሁሉ ነቁ አንድ አዳም ነው ዝቅ ብሎ በደሴት እንዲከፈል እስራኤል በግዝረት አህዛብ በቁልፈት ተለይተዋል በታች ወርዶ በወደብ እንዲገናኝ ህዝብ እና አህዛብ በክርስቶስ ጥምቀት አንድ ሆነዋል፡፡ ብለው አባቶቻችን ካስተማሩን የአንድነት ትምህርት ውጭ የሆነ የሚከፋፍል አስተምህሮ እና ማንኛውንም አይነት ተግባር የሐዋርያውን መልክት በመጥቀስ አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ ( ነገር ግን ወንድሞች ሆይ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትንና ማሰናከያ የሚያደርጉትን ሰዎች እናዳትመለከቱ እለምናችኋለሁ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙም እና እንዳለ ) ሮሜ 16÷17
ሦስተኛ
የሐዋ ሥራ 6÷2 ስለ እስጢፋኖስ እና ስለሌሎች መልዕክተኞች ሹመት በሚናገርበት ክፍል ‹‹ ወንድሞች ሆይ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስ እና ጥበብ የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ ይህም ቃል ህዝቡን ሁሉ ደስ አሰኛቸው እምነት እና መንፈስቅዱስ የመላበት ሰው እስጢፋኖስንና ፊልጶስን መረጡ በሐዋርያትም ፊት አቆሟቸው ከፀለዪም በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው በዚህም የተነሳ ብዙ ሰዎች ለሃይማኖታቸው የታዘዙ ሆኑ ›› ይላል
የዚች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንድነት እና ስርዓት ተጠብቆ ይኖር ዘንድ ይህች ቤተ ክርስቲያን የነበራት ተደማጭነት ወደ ቀደመ ክብሩ ተመልሶ ቤተ ክርስቲያናችን ከኢትዮጵያ ተርፋ በአፍሪቃ በአውሮፓና በሌላም ክፍል ለሚኖሩ የሰው ልጆች በሙሉ እንድምታበራ አንድም ለአለም ጨውና ብርሐን የሚሆኑ በርካታ ልጆች እንድታፈራ ከላይ በጠቀስነው ቃልና እሱን በመሰለው መንገድ በመንፈስ ቅዱስ የተመሉ በመልካም ጠባያቸው የተመሰገኑ የሃይማኖት እና የስነ-ምግባር ጉድለት የሌለባቸው ቅንና ቸር እረኞች በቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት ሊሾምልን ሲገባ የሆነው ግን በተቃራኒ ነው፡፡ ያለ ቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ እና ስምምነት በግለሰቦች ሴራና አምባ ገነናዊነት በአህጉረ ስብከታችን በሲዳማ@ በአማሮ@ በቡርጅና በቦረና የተፈፀመው የሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ሹመት መፅሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነና ስርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ያፋለሰ ወደፊትም የሚያፋልስ ህገወጥ ሹመት እንደሆነ እናምናለን፡፡
ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ
1. የመካነ ኢየሱስ እምነት ድርጅት አባል መሆናቸውን የሚያረጋግጥ በራሳቸው እጅ የተጻፈ ደብዳቤ
2. የቅን ልቦና መንፈሳዊና የፈውስ አገልግሎት የሚባል የእምነት ተቋም በፍትሕ ሚኒስቴር ፍቃድ አውጥተው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው
3. በተራ ቁጥር 2 ላይ የተጠቀሰውን የእምነት ድርጅት በመመስረት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያውክ ሥራ ሲሰሩ መቆየታቸው
4. የተሐድሶን ስራ በስፋት በቤተ ክርስቲያን ስር እየሰሩ ስለመቆየታቸው ለሌላኛው በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ስር ለሚገኝ አጋራቸው የጻፉትን የግል ደብዳቤ እና የመሳሰሉት በመረጃነት እንዳለ እየታወቀ እኚህን ግለሰብ የዚህ ታላቅ አህጉረ ስብከት ሥራአስኪያጅ አድረጎ መሾም ወቅታዊው የቤተ ክርስቲያን ችግር ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ጉልህ ማሳያ ነው፡፡ የሐዋ ሥራ ም 6÷2 በእምነት እና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ይሾም እያለ በምንፍቅና የተጣመመን አካል በቤተ ክርስቲያን ላይ መሾም ምን ይሉታል? መፅሀፉ በህዝብ የተመሰከረላቸው ቅን ሰዎች ይሾሙ ሲል በወንጀል ያሸበረቀን ግለሰብ በቤተ ክርስቲያን ላይ መሾም ምን ይሉታል?
የተወደዳችሁ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች በትንቢተ ዘካርያስ 8÷16ጌታ ‹‹እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋራ እውነትን ተነጋገሩ በበር በአደባባያችሁም እውነትን ፍረዱ›› ብሏል እና ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከባልንጀሮቻችሁ ጋራ እውነት እውነቱን በመነጋገር የዚህ ግለሰብ እና የግብረ አበሮቹ ህገወጥ ድርጊት ድፍረት ከመሆኑም በላይ ሂደቱ ቤተ ክርስቲያንን ለሁለት የሚከፍል ትውልድን የሚገድል በመሆኑ የዚህ ጥፋት
( ምንፍቅና ) ሽፋን@ መሪ@ ተከታይና አስፈፃሚ የሆኑ አካላትን በሙሉ ተባብረን በቃችሁ ልንላቸው ይገባል፡፡
አራተኛ
የአባቶቻችን ፍቃድ የሥጋና የደም ፈቃድ እንዳይደለ ፈቃዳቸው የመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ እነደሆነ እናምናለን በቀደመው ዘመን በነበሩ አባቶች ላይ አድሮ ይህችን ቤተ ክርስቲያን ሲመራ ለተከታዮቿ ስርዓትን ሲሰራ የነበረ ያለ የሚኖር እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ዛሬም በሐዋርያት ስልጣን ቤተ ክርስቲንን በሚመሩ ህዝቡን በሚስተዳድሩ አባቶች ላይ አድሮ ዛሬም እንደትላንት ስርዓት እንደሚሰራ ህዝቡንም እንደሚመራ እናምናለን፡፡በዚህም የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የመንፈስ ቅዱስ አመራርና ውሳኔ ነው ብለን እናምናለን አምነንም እንናገራለን፡፡ ስለሆነም እስከዚህ እለት ድረስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርተን ያጣነው ወደፊትም በመንፈስ ቅዱስ ብንመራ አንዳች የሚጎልብን ነገር የለምና ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ውጭ በቦርድ@ በቡድን ወይም በግል ፈቃድና ፍላጎት ህዝብ እና ቤተ ክርስቲያንን በጉልበት ለመምራት የሚደረግን ማንኛውንም አይነት ጥረት አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ ‹‹እኔ እግዚአብሔር የሚረባህን ነገር የማስተምርህ የምትሄድበትን መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ ›› ኢሳ 48÷17
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን
መረጃዎች በ ከጽሁፉ ጋር አብረው ቢየያዙ ለማስረዳት ትልቅ እገዛ ይሰጣል
ReplyDeleteስለዚህ ይህንን ብታስተካክሉት መልካም ነው
እግዚአብሔር ይችን ቤ/ክ ይጠብቃት
አሜን!!!