Tuesday, May 10, 2011

ይግባኝ ለአጋዕዝት ዓለም ለሥላሴ


ይግባኝ ለክርስቶስ እንደራሴ ለምልዓተ ጉባኤ ለቅዱስ ሲኖዶስ
ውድ አንባቢያን ይህንን ጽሑፍ እንድንጽፍ ያስገደደን የቤተክርስቲያናችን ቋሚ ሲኖዶስ በ27/05/2003 ዓ.ም ያወጣው ታሪካዊው፣አስገራሚው፣ የአቡነ ጳውሎስ ፍፁም አምባ ገነናዊ ጠባይ የታየበት፣ የወይዘሮዋ ከአቡነ ጳውሎስ እና ከሲኖዶስ አባላት ገለል አለማለት የተገለፀበት ቃለ ጉባኤ ነው፡፡
ቃለ ጉባኤውን ደጋግመን ደጋግመን፣ ዓይናችንን እያሸን ደጋግመን አነበብነው፡፡ በመጀመሪያ ማመን አቃተን ቀጥሎ ደግሞ ብዙ ጥያቄዎች መጡብን፤
Ø  እኛ የእነ አቡነ ፋኑአል፣ የእነ መልአከ ሕይወትን እና ሌሎችን ጉዳይ ይዘን ስንመላለስ ለምን ነበር ጉዳያችን በቋሚ ሲኖዶስ እንዲታይ ያልተፈለገው??
Ø  በጣም ብዙ ሕዝብ ተብሎ በቃለ ጉባኤው የተገለፀው በአስር ቅጥቅጥ አይሱዙ መኪና(አንዱ የሚይዘው ሃያ ሦስት አካባቢ የሆነ) የመጣ የተባለው ነው ስልሳ ሰው የመያዝ አቅም ባላቸው አሥራ አራት መኪና የመጣው ሕዝብ ታዲያ የሀዋሳን ምዕመናን አይወክልም የተባለው ለምን ይሆን??
Ø  ምንም ዓይነት የጽሑፍም ሆነ የድምፅ ማስረጃ ሳይቀርብ አጣሪም ሳይመደብ፣ ገና ፊርማቸው ሳይደርቅ አዲስ የተመደቡትን ሥራ አስኪያጅ ማንሳት፤ በጣም ብዙ ለጆሮ የሚቀፍ የቤተክርስቲያን ጉድ የነበሩትን ሥራ አስኪያጅ ግን ማስረጃ በገፍ ቀርቦባቸው ለማንሳት ችግር የነበረው ምን ይሆን??
Ø  መ/ሐዲስ ፍስሃ ለማ ከሌላ ሴት ልጅ እንዳለው የሚያውቁት አቡነ ፋኑኤል፤ ከማወቅም አልፈው ብር እንዲቆርጥላት ማስማማታቸውን ወደ ጎን ትተው ተክሊል በማድረጋቸው ምንም ዓይነት ጥያቄ ሳይነሳ በልጁ ብቻ መወሰኑ ምን ዓይነት የክርስትና ጠባይ ይሆን
Ø  የተማረውን ሕዝብ የያዘው በዩኒቨርስቲ ያለውንም እንዲያስተምር ከራሱ ከሲኖዶስ ፈቃድ ያለው መሆኑን የተረዳነውን ማኅበረ ቅዱሳንን ከአንድ NGO ጋር ማብጠልጠል ለምን ይሆን??
Ø  በቃለ ጉባኤውስ ላይ የቋሚ ሲኖዶስ ፀሐፊ አቡነ ሕዝቅኤል እና አቡነ ጢሞቲዎስ አለመፈረማቸው ለምን ይሆን??
Ø  ምን ነክቷቸው ይሆን አጣሪ ተብለው መጥተው የነበሩ አባቶች 73 ገጽ ማስረጃዎቻችንን ስድስት ሲዲዎቻችንን ወደ ጎን ትተው ዓይናቸውን በጨው አጥበው የሁለት ማኅበራት ጉዳይ ነው ብለው ሪፖርት ማድረጋቸው?? ኧረ ለመሆኑ ሁሉም ማስረጃዎች ሲቀርቡ በቪዲዮ ካሜራ መቀረጻቸውን እረስተውት ይሆን ወይስ አቡነ ጳውሎስንና ወይዘሮዋን ለማስደሰት?
Ø  ይህ ሁሉ መሆኑ የኃጢአታችን ውጤት ይሆን?? በእኛ መሀከል ነውር ይኖር ይሆን? እግዚአብሔር ስለ ኃጢአታችን ክፋት ክፉ አባቶችን ሰጥቶን ይሆን? ወይስ የእኛ ኃጢአት እነሱን ክፉ አደረጋቸው?
Ø  የእኛ ከቤተክርስቲያን መጥፋት፣ ወደየግል ስራችን ማዘንበላችን ይሆን ቤተክርስቲያናችን እንዲህ እንድትሆን ያደረጋት?
ለእነዚህ ጥያቄዎች ሁሉ መልስ ስናጣ ጊዜ የቋሚ ሲኖዶስ ቃለ ጉባዔ እንደ ተራ ነገር በእሰው እጅ ስናየው ጊዜ ይግባኝ ለአጋእዝት ዓለም ሥላሴ ለማለት ተገደድን፤ ወደ መጨረሻው ይግባኝ ሰሚ፤ ፍርዱ እውነተኛ ወደ ሆነው፤ የሰው ፊት አይቶ ወደማያዳላው፤ ፍርዱን ለማስፈፀም የሚከለክለው ዕውቀት፣ ገንዘብ፣ ቦታ፣ ኃይል ወደ ሌለው፤ ልዩ ፍፁም እውነት ወደ ሆነው
ከጥያቄዎች በኋላ ቃለ ጉባኤውን አንድ በአንድ ማየት እና መገምገም ጀመርን፡፡ ውሃ ወደ ላይ አይፈስም ነበር ችግር ሆነብንና አኛም የአባቶቻችንን ቃለ ጉባኤ ወደ መመርመር ገባን፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ክፉ ዘመን እግዚአብሔር ወደ ፊት አያምጣብን
ቃለ ጉባዔው በመጀመሪያ በሲዳማ ሀገረ ስብከት አለመግባባት እንዳለ ያትታል (ምንም እንኳን አመግባባቱ ያለው በሀዋሳ ከተማ ቢሆንም የመንበረ ጵጵስናውና ጉዳዩም ከሀገረ ስብከቱ ጋር ያገናኝልናል ይሁን ብለው ተቀበልነው)፡፡
ጥር 25 ቀን 2ዐዐ3 ዓ.ም አቤቱታ መቅረቡንም ይናገራል ያትታል፡፡ ይኼም ጥሩ ነው ውሳኔው በጥር 27 መሆኑ ይገርማል እንጂ
ችግሩን ለመፍታትም ከዚህ ቀደም በሊቀጳጳስ የሚመራ ልዑክ መላኩንም ይናገራል፡፡ ይኼ እውነት ነው ነገር ግን በቃለ ጉባኤው ላይ እንደተፃፈው ችግሩ በተመሳሳይ መልኩ ሳይሆን መልኩን ቀይሮ ነው የቀጠለው፡፡
የበፊቱ ችግሩ የአስተዳደር በደል ይቅር መልካም አስተዳደር ይስፈን፤ ምዝበራ ይቁም፤ አባቶች አባታዊ ጠባያቸውን ይዘው ይምሩ እንጂ በስድብና በወገናዊነት አይንቀሳቀሱ፣ የጫኑት አስኬማ ይህንን አይፈቅድላቸውም ነበር፡፡
የአሁኑ ግን እነ እገሌ መድረክ ላይ ያስተምሩ፣ እኛ ቤተክርስቲያኑን እናስተዳድረው ወዘተ ናቸው፡፡
ቀጥሎም ስለ አጣሪ ልዑኩ ሪፖርት ይናገራል፡፡ አጣሪ ልዑኩም ከቀረቡለት ሠነዶች፣ መረጃዎች እና በራሱ አካሄድ የደረሰበት ጭብጥ ብሎም የችግሩ ዋነኛ መንስኤ ተስፋኪዳነምሕረት የልማትና ፀረ ኤድስ ማኅበርና ማኅበረ ቅዱሳን ናቸው ይላል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በሲኖዶስ የፀደቀ መተዳደሪያ ያለው ስለሆነ ወደ ጎን እንተወውና ለመሆኑ ተስፋኪዳነ ምሕረት ማነው? የሚለውን እንይ
ተስፋ ኪዳነ ምሕረት NGO ማኅበር ማለት የሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የሰንበት ተማሪ በነበሩና በሆኑ ልጆች በኤች አይ ቪ ዙሪያ በመስራት እራሳቸውን ለማስተዳደር የመሠረቱት ማኅበር ነው፡፡
በእንቅስቃሴያቸውም በአንድ ወቅት በቤተክርስቲያኒቱ ስም ሕገወጥ ማኅተም አስቀርጸው በመንቀሳቀሳቸው በሀገረ ስብከት ደረጃ የታገዱ፤ በሁዋላም በወቅቱ የነበሩት ሥራ አስኪያጅ ጳጳስ ሆነው ሲሄዱ አዲስ ከተመደቡት ሥራ አስኪያጅ ጋር በገንዘብ በመመሳጠር በቤተክርስቲያን ዙሪያ እንቅስቃሴ የጀመሩ እና በኋላም ባደረጉት ተደጋጋሚ ጥፋት በቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሰበካ ጉባኤ አሳሳቢነት በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ለሁለተኛ ጊዜ የታገዱ ናቸው፡፡
ታዲያ ተስፋ ኪዳነ ምሕረት ሁለት ጊዜ ከቤተክርስቲያን የታገደ ከሆነ እንዴት በሕዝቡ ጥያቄ ውስጥ ገባ የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ የገባው እንዲህ ነበር፡
ሕዝቡ በተለይ የቅዱስ ገብርኤል ገዳም ልማት ኮሚቴ በወቅቱ በነበሩት ሥራ አስኪያጅ ላይ ጥያቄ አንስቶ ከሊቀ ጳጳሱ ምንም ምላሽ እጥቶ ተቸግሮ በነበረበት ጊዜ ተስፋ ኪዳነ ምሕረት NGO ማኅበር እግዱ ሳይነሳለት በመስቀል አደባባይ ጉባኤ አዘጋጀ፤ የአርባ ሺ ብር ስፖንሰር ጥያቄም ለባለሀብቶች ማደል ጀመረ፡፡ ይህ ሁኔታ ሲታወቅ የሦስት አብያተ ክርስቲያናት ሰበካ ጉባኤዎች በሕብረት ለጠቅላይ ቤተክህነት በማሳወቅ ጉባኤው እንዲቀር ተደረገ፡፡ በዚህን ኒዜ የአስተዳደር በደል ጥያቄውን በወቅቱ የነበሩት ሥራ አስኪያጅ በተስፋ ኪዳነ ምሕረት ማኅበር ጋር እና ከእነ ያሬድ፣ በጋሻው ግሩፕ ጋር ለማያያዝ ቻሉ፡፡
ተስፋ ኪዳነ ምሕረት NGO ማኅበር ግን ከዚህ በኋላ እንደ ማኅበር በእንቅስቃሴው ውስጥ የተሳተፈበት ጊዜ የለም፤ ነገር ግን አባላቱ የሚያገኙት ጥቅም ስለተነካ እንደቤተክርስቲያን ልጅነታቸው በሰንበት ት/ቤት ያላቸው ድርሻ ተጠቅመው በእነ አቡነ ፋኑኤልና መልአከ ሕይወት እንዲሁም በእነ ያሬድ አደመ በመታገዝ የእነሱ ደጋፊ ሁነው ተነሱ እንጂ እንደ ማኅበር አባላቱ ተስማምተው የተንቀሳቀሱበት ሂደት አልነበረም፡፡ የጉዳዩ አቀጣጣይ ሆኑ እንጂ የጉዳዩ አካላትም አልነበሩም፡፡
አጣሪ ልዑኩ ግን በየት አምጥቶ የነገሩ መነሻ እንደአደረጋቸው በጣም እንቆቅልሸ ነው፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን ደግሞ የሚለይ ነው፤ በጉደዩ አለበት ካሉ ሀዋሳ ያለውን ማዕከል አነጋግረው ወይም አዲስ አበባ ያለው አወያይተው ማወቅ ሲችሉ እንዲሁ በነሲቡ እነ ያሬድ አደመ ይህንን የሚያደርግ ማኅበረ ቅዱሳን ነው በማለት የአቡነ ጳውሎስን ጥላ ለማግኘት የተጠቀሙበትን መፈክር በመውሰድ ማኅበረ ቅዱሳን ነው ማለታቸው አጀብ ነው
እስኪ ይሁንና ተስፋ ኪዳነ ምሕረት እና ማኅበረ ቅዱሳን በምን ተጋጩ፣ ሪፖርቱ ውሸት አይታክተው እንዲህ ይላል
‹‹ተስፋ ኪዳነ ምሕረት ማኅበር ከልዩ ልዩ ሰባኪያንና ዘማሪያን ባለው መቀራረብ መስቀል አደባባይ ጉባኤ ሲያስፈቅድ›› ይላል ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና ደጋፊዎቻቸው ስላልተደሰቱ እና የቤተክርስቲያኗን መድረክ እጅ ለማድረግ›› ይላል
እስኪ አጣሪ ልዑካን እንጠይቃችሁ ለመሆኑ የመስቀል አደባባይ ጉባኤን ማን አገደ በማን ጥያቄ? ከየት አምጥታችሁት ነው የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ያላችሁት? የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የቤተክርስቲያኑቱ ልጆች ናቸው ወይስ ሌላ?
ኸረ ለመሆኑ ጉባኤው ለምን ታገደ ብላችሁ ማጣራት ያልሞከራችሁት ለምን ይሆን? የቤተ ክርስቲያኒቱን መድረክ እጅ ለማድረግ የመስቀል አደባባይ ጉባኤን በማስከልከል ሆነ እንዴ? ‹‹መድረክ ለመያዝም የሞት ሽረት ፍልሚያ›› እንዳለ አድርጋችሁ ሪፖርት አደረጋችሁ ከየት አግኝታችሁት ይሆን? በጣም እርግጠኞች ነን በ73 ገጽ ማስረጃዎቻችንም ሆነ በስድስት ሲዲዎቻችን ስለመድረክ ጥያቄም ሆነ ሀሳብ አልነበረንም ከየት መጣ? ልዑካን፣ እነ አቡነ ፋኑኤልና  መልአከ ሕይወት ፀሐይ መላኩ ስለተነሱ ነገር ለማድበስበስ ይሆን? ወይስ አቡነ ጳውሎስን ለማስደሰት እና በሀዋሳ ሰላም እንዳይኖር ከመፈለግ?
ቀጥላችሁም ከቃለ ጉባኤው እንደምንረዳው ከሳሾች አላችሁን ምን ዓይነት ጠባይ ያላችሁ ኦርቶዶክሳዊ አባቶች ናችሁ፡፡ ስለቤተክርስቲያን መቆም አስተዳደራዊ በደል አለማለት፣ ምዝበራ ይቁም ማለት፣ አባታዊ ጠባያችሁን አክብሩት ማለት በየትኛው አንቀጽ ይሆን ከሳሽ የሚያስብል? ነው ወይስ ነግ በእኔ ብላችሁ ነው?
አቡነ ጳውሎስስ ልብዎት ያውቅ የለም እንዴ፤ እንደሚያስተውሱት አቡነ ፋኑኤል አሜሪካ እያሉ የልማት ኮሚቴው እርሶ ጋር ሲመጣ ከልማት አጀንደው ባሻገር የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ችግር እንዳለበት፡፡ አቡነ ፋኑኤል ከአሜሪካ ከመመለሳቸው በፊትም ሀዋሳ ለመምጣት ያሳዩት ፍላጎትን ረሱት እንዴ?
ወይዛዝርቱስ ቢሆኑ ከእነ በጋሻው ተልከው መጥተው በወቅቱ የልማት ኮሚቴው የመስቀል አደባባይን ጉባኤ የማስቆም አላማ እንደሌለው እንደማያውቀው የተነጋገርነው ረሱት እንዴ?
ሌሎቻችሁስ በዚህ ውስጥ ያላችሁ ስልክ በደወላችሁ ጊዜ የልማት አጀንዳ እንጂ ሌላ እንደሌለን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እንጂ ሌላ እንደሌለ የተወያየነው ተረሳ? ነው ወይስ ምን ያለበት ዝላይ አይችል ሁኖ ነው ነገሩ?
አቤት አጣሪ ልዑካን ስንቱ ይታዘባችሁ!! ዛሬ እኛን ከሳሽ ስትሉ፡፡ እግዚአብሔርስ እንዴት ያዝንባችሁ?
ቃለ ጉባኤው በመቀጠል ‹‹በተስፋ ኪዳነ ምሕረትና ማኅበረ ቅዱሳን በማይመለከታቸውና በማያገባቸው በቤተክርስቲያናችን አስተዳደር ጣልቃ እየገቡ የራሳቸውን ፋላጎት ለማሳካት›› ይላል
በተስፋ ኪዳነ ምሕረት በእርግጥ ቢቻል ከዚህ ቀደምም ያደረገው ስለሆነ እና ከቤተክርስቲያን መዋቅር ውጪ ስላለ ጣልቃ የሚለው ይስማማዋል፡፡ ራሳችሁ ያደራጃችሁት ደንብ የሰጣችሁት እና በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ያስቀመጣችሁት ኸረ ለመሆኑ እንዴት ሁኖ ነው ጣልቃ ገብ የራሱን ፍላጎት የሚያስፈጽም የተባለው? ለመሆኑ ፍላጎቱ ምን ይሆን?
ከውሳኔ ሀሳቡ በፊት ቃለ ጉባኤው ‹‹… የቤተ ክርስቲያናችን ክብርና መብት ሲደፈር ቅዱስ ሲኖዶስ በአርምሞ ሊመለከት አይችልም….›› ይላል፡፡ በጣም ደስ የሚል፣ የሀይማኖት ስሜት ያለው አገላለፅ ነው፤ በድርጊት አልታየም እንጂ
አባቶቻችን ኽረ ለመሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን ክብር መደፈሩ ስድስት ወር ከዚህ ቀደም ስንንገላታ ያልታያችሁ ፤የአጣሪው ሪፖርት ተደብቆ ቆይቶ በዚህ ሰዓት ለቋሚ ሲኖዶስ ሲቀርብ ይሆን የታያችሁ፤ ለመሆኑ ስርዓት ይከበር፣ ምዝበራ ይጥፋ፣ የአባት ጠባይ ይከበር ማለት ነው የቤተ ክርስቲያንን መብት እና ክብር መድፈር ወይስ ለግል ጥቅም ሰዎችን ማደራጀት
የሀዋሳ ጉዳይ እንዳይፈታ የሲኖዶሱን ክብርና መብት በመድፈር ከአቡነ ጳውሎስ ጋር በመጣበቅ ነገር እያጦዘች ያለችው ወይዘሮ ነች በአርምሞ ልትታይ የማይገባት ወይስ የቤተክርስቲያንን ክብር ተደፈረ፣ ቤተክርስቲያን የወንበዴዎች ዋሻ ሆነች እያለ ያለው፡፡
ይሁን እስኪ አባቶቻችን ለክብርና ለመብት መቆም ጥሩ ነው (ስታደርጉት ባናይም)፡፡ ግን ምነው በአንድ ወገን ያለውን ብቻ ሰምታችሁ በሌላ ወገን ያለውን ሳትሰሙ ለመወሰን ተነሳችሁ? እንዳናምናችሁ ስለምትፈልጉ ነው ወይስ አባት እንድንጠላ እና ከቤተክርስቲያን እንድንርቅ ይሆን፡፡
መረሳት የሌለበት ግን አባቶቻችን ሻጮችንና ለዋጮችን በጅራፍ ገርፎ የሚያስወጣ አምላክ እንዳለ ያስተማራችሁን ነው፡፡
በስተመጨረሻ የቃለ ጉባኤውን ውሳኔ ደግሞ እንየው፡፡ ቃለ ጉባኤው ዘጠኝ ውሳኔዎች ይዟል
የመጀመሪያው አዲስ የሰበካ ጉባኤ፣ የሰንበት ት/ቤት እና የስብከተ ወንጌል መቋቋም እንዳለበት ተገቢ ባልሆነ ሁኔታም ቢሆን ያትታል፡፡ ይህ እኛም የምናምንበት የታገልንበት ሁሉንም ችለን እርቀ ሰላም ያወረድንበት ጉዳይ ነው፡፡
ሁለተኛው ስለጣልቃ ገብነት፣ ሶስተኛው ስለቅዱስ ሩፋኤል፣ አራተኛው ስለህንፃዎችና ተሸከርካሬዎች ያትታል፤ ለሌላው አጫፋሪ ለመሆን እና በአጣሪ ልዑኩ ሪፖርት መሠረት ነው የወሰነው ለማለት ይመስላል
ከዚህ ቀደም እኛ ስለ ቅዱስ ሩፋኤል ያነሳውን፣ ስለ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን መኪና ያነሳነው ምን ያክል ያስተዳደር ብልሹነት እንዳለ ለማሳየት መሆኑ ተረሳና ከሳሽ ተባልንበት፤ ሚዛናዊ ለመምሰል እና ውሳኔ ዘጠኝን ለማለዘብ ተወሰነ
አምስተኛው ስለ ገለልተኝነት ይነገራል፣ ስድስተኛውም ስለአንድ ግለሰብ ያትታል፡፡ ይሁን አንቃወምም
ሰባተኛው ስለ አውደ ምህረቱ ይናገራል ‹‹ እስከዚያው ድረስ የደብረ ምህረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ሆነው በሚሰሩት መላከ ምህረት ጳውሎስ ቀፀላ ‹‹ እንዲከናወን ይነገራል ይኼም ጥሩ ነው
ስምንተኛው ለማረጋጋት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እንደሚላኩ ይናገራል እንኳንስ ብፁአን ሊቃነጳጳሳት ሊመጡ ይቅርና የተመደቡትን ሊቀ ጳጳስም አቡነ ጳውሎስ ይደበደቡዎታልና እንዳይሄድ ብለው አስቀሩዋቸው፡፡
እሳቸው /አቡነ ጳውሎስ/ የሚደግፉዋቸው በወይዘሮዋ የሚታገዙት ክፍሎች ተደባዳቢ መሆናቸውንም አቡነ ጳውሎስ በእርግጥም አሳምረው ያውቃሉ፡፡ በዱላ የሚያምን ኦርቶዶክሳዊ ደግሞ ምንም የለም
ዘጠነኛው ስብሰባው በዋናነት የተሰበሰበበት በሚመስለው ውሳኔ ደግሞ ሦስት ወር በቅጡ ያልሞላው አዲሱ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ስለመነሳታቸው ይነገራል
ለመነሳታቸውም  ምክንያት ሁኖ  የቀረበው ጥር 25/2005 በቀረበው አቤቱታ ይላል
ለመሆኑ በየትኛው ሳይንስ ወይስ ሃይማኖት ይሆን አቤቱታ ሳይጣራ ውሳኔ የሚሰጥበት፤ ያውም በሀገረ ሰብከት ስራ አስኪያጅ ላይ፤ ለዚያውም ከተመደቡ ሶስት ወር ሳይሞላቸው፣ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሳያምኑበት፡፡ ምን ዓይነት ውሳኔ ነው አባቶቻችን እየወሰናችሁ ያላችሁት ተገንዝባችሁታል
ያለ ደብራቸው እየመጡ ህዝቡን እያወኩና ወደ ማይገባ ቅራኔ ለመክተት ‹‹ያለነውጥ ለውጥ አይመጣም….›› እያሉ ሰበክን የሚሉት አስተዳዳሪዎች ተቀምጠው፤ ያለ ስልጣናቸው ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ላልተፈቀደላቸው ሰዎች የመስበክ  የመዘመር ፈቃድ የሰጡት አስተዳዳሪ ተቀምጠው የሥራ አስኪያጁ መነሳት እንኳን በሀይማኖት ላለ በዓለምም ደረጃ እግዚኦ መሐረነ የሚያስብል ነው፡፡
ጳጳስ በሀገረ ስብከቱ እንዳይቀመጥ ላደረጉና እንደሚደባደቡ በፓትርያርኩ ለተመሰከረባቸው ሰዎች ሲባል፣ ለወይዘሮዋ ሲባል የሀገረስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ማንሳት በእውነቱ ታሪክ ነው፣ ጉድ ነው፡፡
በሀገሩ ሰው ጠፍቶ፣ እግዚአብሔርም ካኃጢያታችን የተነሳ ወይም ለፅድቅ ዝም ብሎ የሲኖዶስ ውሳኔዎች በሴቶች ሲበላሽ ከማየት የከፋ ምን ይኖር ይሆን?
አባቶቻችን የቋሚ ሲነኖዶስ ቃለ ጉባኤና ውሳኔ ተብሎ በተሰራጨው በጣም አፈርን፣ አዘን፣ጉድ አልን፡፡ የውስጣችሁ ውሳኔ እንዳይሆን ፀለይን ነገር ግን በመፈረማችሁ ዝም በማለታችሁ ነቀፍናችሁ፣ አባት ብሎ ለመጥራት አፈርን፣ አንገታችንን ደፋን፡፡ በውስጣችን ግን
          ‹‹ፅዮን ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፣ ባላስታውስሽ ምላሴ ከትናጋዬ ይጣበቅ›› አልን
እግዚአብሔር አገራችንን ይባርክ
ቤተ ክርስቲያንችንን ይጠብቅ
ቀን 07/07/2003

2 comments:

  1. Good evidence, but it seems from the reflection that all Fathers of the church were not in a position to lead the church,I hate this over generalization,the other thing is you have assured that, those "Mafias" are members of our church by saying:"ተስፋ ኪዳነ ምሕረት NGO ማኅበር ግን ከዚህ በኋላ እንደ ማኅበር በእንቅስቃሴው ውስጥ የተሳተፈበት ጊዜ የለም፤ ነገር ግን አባላቱ የሚያገኙት ጥቅም ስለተነካ እንደቤተክርስቲያን ልጅነታቸው በሰንበት ት/ቤት ያላቸው ድርሻ ተጠቅመው በእነ አቡነ ፋኑኤልና መልአከ ሕይወት እንዲሁም በእነ ያሬድ አደመ በመታገዝ የእነሱ ደጋፊ ሁነው ተነሱ እንጂ እንደ ማኅበር አባላቱ ተስማምተው የተንቀሳቀሱበት ሂደት አልነበረም፡፡ የጉዳዩ አቀጣጣይ ሆኑ እንጂ የጉዳዩ አካላትም አልነበሩም፡፡However,I believe that they are not children of the church.The you made on is good in the remaining part,ketilubet.
    ‹‹ፅዮን ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፣ ባላስታውስሽ ምላሴ ከትናጋዬ ይጣበቅ›› አልን
    እግዚአብሔር አገራችንን ይባርክ!
    ቤተ ክርስቲያንችንን ይጠብቅ!

    ReplyDelete
  2. ውድ ምእመናን ቤተክርስቲናችንን ከአውሬዎች ምንጠብቅበት ሰዓት አሁን ነውና ነቅትን ልንጠብቅ ይገባናል
    የነአቡነ ጳውሎስ ፣ፋኑኤል፤ጌታቸው ዶኔ(ፈዋሹ) ፤በጋሻው ደሳለኝ(ተኩላው) ያሬድ አደመ (ተላላኪው) ወይዘሮዋ(አገናኝ) ተስፋ ኪዳነምህረት ማህበር ስር የተጠለላችሁ ጥቂት ወንበዴዎች ስማችሁ በየተራ የተጠቀሳችሁ መናፍቆች እጃችሁን ከቤተክርስቲን ላይ እንድታነሱ በወላዲተ አምላክ ስም አማጸናችዋለሁ፤፤
    እግዚህአብህር ቤተክርስቲያናችንን የጠብቅልን

    ReplyDelete